2022-05-26 10:48:10
በአማራ ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን በክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሕዝቡ ቀልጣፋና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በባሕር ዳር የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞችን በማነቃቃት ኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ.ር) በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት፣ በርካታ ወገኖች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል።
በሽብር ቡድኑ ምክንያት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመዘረፋቸውና በመውደማቸው የመንግሥት አገልግሎት ተስተጓጉሎ መቆየቱን ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ በኅብረተሰቡና በጸጥታ አካላት ርብርብ የተወረሩ አካባቢዎች ነፃ በመውጣታቸው የመንግሥት አገልግሎት ተመልሶ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺአምላክ ገብረማርያም ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ በአማራ ክልል 417 ሺህ በላይ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች እንደሚገኙና በሚፈለገው መሰረት አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን አመላክተዋል።
አብዛኛኞቹ ተቋማት ብልሹ አሠራር እንደሚታይባቸው ነው የጠቆሙት። የሄም ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ እያደረገው ነውም ብለዋል።
ወይዘሮ ባንቺአምላክ እንዳሉት በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ባለሙያው በአግባቡ ሥራውን እንዲያከናውን መደገፍ፣ ማበረታታትና መገምገም ይጠበቅባቸዋል።
በርካታ ባለሙያዎች ሥራቸው በአግባቡ ሳይመዘን አላስፈላጊ የውጤት ተኮር እንደሚሞላላቸው ኮሚሽነሯ አስረድተዋል። ስለሆነም እነዚህ ተቋማት ከግዴለሽ አሠራር ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። ተቋማት በስታንዳርድ የተቀመጠውን ተግባር መፈጸም እንዳለባቸውም ወይዘሮ ባንቺአምላክ ገልጸዋል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሠራተኞቻቸው የመንግሥትን የሥራ ሰዓት እንዲያከብሩ፣ መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁና እንዲፈጽሙ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ለክልሉ እድገት አመራሩና ባለሙያው ተግባብቶና ተደጋግፎ መሥራት እንዳለባቸው ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
በክልሉ ለሕዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት:-
የሥራ ባሕልን መቀየር
የጊዜ አጠቃቀምን ማሻሻል
ምርትና ምርታማነትን መጨመር
ባለሙያውና የሥራ ኀላፊዎች ችግርን በመቋቋምና ተናብቦ ኅብረተሰቡን ማገልገል
ተጠያቂነትን መዘርጋት
ማበረታቻን መስጠት
ብልሹ አሠራርን መታገልና ማስወገድ
ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት ተጠቃሽ መፍትሔ እንደሆነ በንቅናቄ መድረኩ ተነስቷል።
ሠራተኛውንና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ለማትጋት ያለመ የንቅናቄ መድረክ በክልሉ በየደረጃው የሚካሄድ እንደሆነም ተመላክቷል። አሚኮ
189 viewsAlemshet, 07:48