Get Mystery Box with random crypto!

'የአማራ ሕዝብ ሕግና የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚፈልግ፤ ለሕግና ሥርዓትም ቀናኤ የኾነ ሕዝብ ነ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

"የአማራ ሕዝብ ሕግና የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚፈልግ፤ ለሕግና ሥርዓትም ቀናኤ የኾነ ሕዝብ ነው" የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን

ባሕርዳር: መጋቢት 27/2015 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የአማራ ሕዝብ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ላይ በሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ላይ ያተከረ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።

ውይይቱ ከዓቃቢያነ ሕጎች ፣ከዳኞች ፣ከጠበቆችና ከዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁራን ጋር ነው ሲካሄድ የቆየው።

ዩኒቨርሲቲው ከውይይቱ የተገኙ ግብዓቶችንና የጥናት ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ሪፖርት አቅርቧል።
በመድረኩ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት እሰይ ከበደ (ዶ.ር) በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ከአማራ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር ብሎም በሀገራዊ ግንባታው ጠቃሚ ግብዓት ለመስጠት ነው የሕግ ትምህርት ቤቱ ምሁራን ከአጋር አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ያካሄዱት ብለዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ጥናትን መሰረት ያደረገ በሀገር መሰረታዊ ውቅር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ የላቀ አበርክቶ እያረገ እንደኾነም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ሕግና የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚፈልግ፣ለሕግና ሥርዓትም ቀናኤ የኾነ ሕዝብ ነው ያሉት ዶክተር እሰይ አሁን በሥራ ላይ ባለው በኢፌዴሪ ሕገ- መንግስት ከመብትና ማንነት፣ከልማት ተጠቃሚነት እስከ ፍላጎቱና ጥቅሙን የሚያስከበርለት የሕግ ሥርዓት እንዳልተዘረጋለት ያምናል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የጸጥታና የደኅንነት ጉዳይ በዙሪያው የሚደርስበት ትንኮሳ እርፍት እየነሳው፣ ባልተመለሱለት የማንነት ጥያቄዎችም የሚዋከብ ሕዝብ ኾኗል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ተመስገን ሲሳይ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ከጅምሩ የረቀቀበት ፣የጸደቀበት አጠቃላይ ሁኔታና አሁን የሚነሳበት የቅቡልነት ጥያቄ ላይ ያተኮረ የጥናት ሪፖርት አቅርበዋል።

የሕግ መምህሩ ተመስገን ሲሳይ እንዳሉት ማንነትን መሰረት አድርጎ የተመሰረተው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የአማራን ሕዝብ በማንነቱ በሚገባ ያልወከለና ያላሳተፈ ነው ብለዋል።

ዛሬ ላይ በየሁኔታው እንደ ሕዝብ የሚደርስበት ወከባም በልኩ የሚወክለውና መብትና ጥቅሙን የሚያስከብርለት ሕገ- መንግሥት ያለመኖር ውጤት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ሕገ- መንግሥቱ ሲረቀቅም ኾነ ሲጸድቅ አማራን በሚገባ የሚወክል ፣ፍላጎቱንና ጥቅሙን የሚያስከብር ተወካይ እንዳልነበረው ባቀረቡት የጥናት ሪፖርት አመላክተዋል። እንዲህ አይነት ውይይቶች የአማራ ሕዝብ ለምን የሕገ-መንግሥቱን መሻሻል ይፈልጋል፣ እንዴትስ እንዲሻሻል ይፈልጋል የሚሉ ነጥቦችን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለማቅረብ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በመድረኩ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ (ለውጥ) እንዲደረግ ግድ የሚሉ ጉዳዮችና ማሻሻል ሥራው ሊተኮርባቸው የሚገባቸው ነጥቦች ላይ ያተኮረ የጥናት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ከመርሐ ግብሩ መረዳት ተችሏል።

የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የዛሬው የውይይት መድረክ የጥናት ሪፖርቱን ተደራሽ ለማድረግ ፣ለማዳበርና በቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ ለማስቀመጥ የሚያስችል ነው ተብሏል።
አሚኮ