Get Mystery Box with random crypto!

ካዳስተር ማለት ምን ማለት ነው? ካዳስተር ማለት መሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥር | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

ካዳስተር ማለት ምን ማለት ነው?

ካዳስተር ማለት መሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ሲሆን የሚደራጁት መረጃዎችም በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ይኸውም የካርታ መረጃ (spatial data) የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ገላጭ መረጃ (non-spatial data) በመባል የሚታወቀው የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ.)፣ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ፣ ወዘተ… እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሁለት የመረጃ ዓይነቶችም በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡

ካዳስተር በሦስት ዓይነት ይከፈላል፡- አንደኛው ህጋዊ ካዳስተር ሲሆን ለእያንዳንዱ ህጋዊ ወሰን ለተለየለት ይዞታ፣ የይዞታ መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት የሚያመለክት መረጃ ከይዞታው ካርታ ጋር አጣምሮ የያዘ ወቅታዊ የመሬት ይዞታ መረጃ ሥርዓት ሲሆን አስፈላጊነቱም ዬትኛው ይዞታ በማንና በምን አግባብ ተይዟል የሚለውን በማጣራት የባለይዞታውን የይዞታ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ፊስካል ካዳስተር ሲሆን በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዝ ሆኖ ለቦታና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ካዳስተር ሁለገብ/ሁሉን አቀፍ ካዳስተር/ የሚባለው በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የተገለፁትን መረጃዎች የሚይዝ ሆኖ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓት ነው፡፡

የካዳስተር ሥርዓት በመገንባት ሂደት በርካታ ልምድ ያላቸውና ብዙ ርቀት የሄዱ አገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚህ የግንባታ ሂደት እያንዳንዱ አገር ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አጀማመሩና አካሄዱ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ከፊስካል ካዳስተር ጀምረው ወደ ሁለገብ የሄዱ አሉ ለምሳሌ ፈረንሳይ፤ ሌሎች ደግሞ ከህጋዊ ካዳስተር ጀምረው ወደ ሁለገብ የካዳስተር ሥርዓት የተሸጋገሩበት ሁኔታም አለ ለምሳሌ ኔዘርላንድ፡፡ በእኛ አገር ደረጃም ከዚህ ቀደም በከተማ ደረጃ ሥርዓቱን ለመዘርጋት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የተሞከሩትም ሁለገብ ካዳስተርን በመዘርጋት ነበር ሆኖም ግን የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣና የሥርዓቱን ዘለቄታዊነት የሚያረጋግጥ ሊሆን አልቻለም፡፡

በመሆኑም በቅድሚያ ባለይዞታውን ተጠቃሚ የሚያደርገው ከተማ አስተዳደሮችም መሬታቸውን ቆጥረው ሊያውቁ የሚችሉበትን የህጋዊ ካዳስተር በመዘርጋት በመቀጠልም የፊስካል ካዳስተር ብሎም ወደ ሁለገብ ካዳስተር የሚያድግ ሥርዓት መዘርጋቱ ሥርዓቱን ቀጣይ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ተመርጧል፡፡

በዚህ ሂደት የካርታው መረጃ አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ ሲሆን ለውጥን ተከትሎ ወቅታዊ ማድረግ የሚያስፈልግ ሆኖ ሁሉም የካዳስተር ዓይነት መሰረት የሚያደርገው በህጋዊ ካዳስተር የተዘጋጀውን የካዳስተር ካርታ ነው:: ሌሎች መረጃዎች ተደማሪ እየተደረጉ ወደ ሁለገብ ካዳስተር ሥርዓት የሚያድግ ይሆናል፡፡