Get Mystery Box with random crypto!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ ከዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ ጋር | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ ከዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለተቋሙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የአመራር ክህሎት እና ስትራቴጂያዊ አስተዳደር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል

የስልጠናው ዋና ዓላማ የተሻሻለ የህግ ሥርዓት እንዲኖር ማስቻል እና የፍትሕ ተቋማት በሙያ ተመስርተው እና ሕግን መሰረት አድርገው እንዲሰሩ ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠና መድረኩ ላይ የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዝግአለ ገበየሁን ጨምሮ የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ በላይ፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የምድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪዎች፣ የዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊዎች፣የሪጂኦ ፖሊታን ፍትሕ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣የሂደት መሪዎች፣ዐቃቤያነ ሕግ በስልጠናው ታድመዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዝግአለ ገበየሁ የስልጠናውን ዋና ዓላማ አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በንግግራቸው ወቅት ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን የፍትህ ሥርዓቱን ለማዘመን ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በፌዴራል ፍትህ ሚንስቴር እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የፍትህ ተቋማት ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ልዩ ልዩ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና የፋይናንስ ድጋፍ ጭምር በማድረግ ለፍትህ ስርዓቱ መዘመን ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በተቋቋመው የአስፈፃሚ አካላት መመሪያ 280/2014 ዓ.ም መሰረት ቢሮው የአደረጃጀትና የአሰራር ማኑዋል ክለሳ ማካሄዱን ገልፀዋል። በዚህ ክለሳ መሰረትም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ በርካታ የፍትህ አመራሮችን አወዳድሮ መመደብ መቻሉን ጨመረው ገልፀዋል።

በመሆኑም የአዲሱን አመራር ክህሎት ለማዳበር እና የአመራር ክፍተቶችን ለመሙላት ተከታታይ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልፀው የዛሬው ሥልጠናም በዕውቀት እና ክህሎት የዳበረ አመራር በመፍጠር በአገልግሎቱ ህዝብን ማርካት የሚችል ብቁ መሪ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ማንደፍሮ በላይ በበኩላቸው በ2010 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በኋላ በፍትሕ ተግባራት ዙሪያ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ምክትል ኃላፊው አያይዘውም ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የሕግ ተቋማት ለማጠናከር፣ የትምህርት ካሪኩለም እና ጥራት፣ የህግ ሪፎርም የቴክኒክ ሥራ እና ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት ላይ በርካታ ሥራዎችን በመስራት የመንግስትን ወጭ በመሸፈን ትልቅ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።

መመሪያዎችን እና አዋጆችን በተመለከተ ቴክኒካዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው የሲቪል እና የሚዲያ ተቋማትን ጭምር ለማጠናከር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።

የዛሬው ሥልጠና የዚህ አካል መሆኑን ገልፀው ሰልጣኞቹ ስለ ሥራ አመራር ፅንሰ ሃሳብ፣ ስለ አመራርነት ጥበብ፣ ስለ አመራር ማይንድ ሴት፣ ስለ ለውጥ ተኮር የአመራር ዘዴ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ መምራት ጥበብ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል። በቀጣይ ፕሮጀክቱ በቆይታው ያመጣው ውጤት በገለልተኛ አካል እንደሚገመገም እና አስተያዬት እንደሚሰጥበትም ጨምረው ተናግረዋል።

አመራሮች በየጊዜው በቴክኒክ እና በክህሎት እራሳቸውን ማዳበር ስለሚገባቸው እንዲሁም አንድ አመራር ወደ መሪነት ከመምጣቱ በፊት ብቁ ሆኖ መገኘት ስላለበት በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ በቂ እና ቋሚ የአመራር ማሰልጠኛ ተቋም መኖር እንደሚገባውም አስተያዬት ሰጥተዋል።
APP