Get Mystery Box with random crypto!

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የአማራ ክልል ትብብር ጥምረት የተከናወኑ ተግባራት የሚገመግም መድረክ ተካሄደ።
(የካቲት 14 ቀን 2015ዓ.ም) መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ ገረመው ገብረጻድቅ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በክልሉ ውስጥ ያለውን በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል መከላከልና ምላሽ መስጠት በተመለከተ ባለፉት ጥቂት አመታት የተለያዮ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ይሄን ወንጀል ለመከላከል የወጣውን አዋጅ መሠረት በማድረግ የተቋቋሙ ስድስት የስራ ቡድኖች ሕግ መከላከሉ፣ መልሶ ማቋቋሙ፣የማህበረሰብ ውይይት ፣የስልጠና የምርምር፣ የዲያስፖራ ጉዳዬች ቡድኖች ባለፋት ስድስት ወራት ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ይሄንን ደግሞ በበላይነት የሚያስተባብረው በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሚመራ ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ኘሬዚዳንት የሆነ ምክር ቤት እንዲኖር በአዋጁ የተቋቋመውን ወደ ተግባር ለማስገባት በሂደት ያለ መሆኑን አውስተው ከርሱ በመለስ ያሉ ተግባራት እየተከናወኑ በአገር ደረጃ ላለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለሚመሩት አገራዊ የትብብር ጥምረት ጭምር የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት እያቀረበ እየተገመገመ ነው፡፡ አያይዘውም በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል በክልላችን ላይ በኢኮኖሚም በማህበራዊም የሚኖረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያስከትል ግዙፍ ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ይሄን ወንጀል ለመከላከልና ምላሽ ለመስተት በቅንጅት ምላሽ መስጠት ካልተቻለ የፀጥታም፣የደህንነት ስጋት እየሆነ ነው የመጣው፡፡በስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን መነሻ በማድረግ ለቀጣይ እንዴት ባለ መንገድ ተቀናጅተን እንሰራለን በሚል ተወያይተን በየድርሻችን ባደገ ሁኔታ ወደ ተግባር መግባት አለብን ብለዋል፡፡
ስለዚህ በክልላችን በሁሉም ዞኖች ላይ የዚህ ተግባር ምልክቶች ቢኖሩም፣ክልሉ መነሻ ፣የሌሎች ክልሎች፣የጎረቤት አገራት ጭምር ማቋረጫ መሸጋገሪያ እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡በዚህ ልክ ከፍ አድርገን እየገመገምን እንዴት እንፍታው በማለት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በክልላችን በሁሉም ዞኖች ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ስለዚህ ይሄንን ለመከላከል ዋና ዋና አካባቢዎችን ለይተን ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ በምስራቁ ቀጠና ፣በምዕራብ ቀጠና ምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር በ25 ወረዳዎች ላይ በ86 ቀበሌዎች ላይ በቀበሌ ጭምር ችግር ያለባቸው ተለይተዋል፡፡
የመከላከሉ ተግባሩን እየሰፋ በየቀበሌው በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ከማሻገር ነፃ የሆነ ቀበሌ መፍጠር በሚል መሪ መልዕክት ይዘን በንቅናቄ ችግሩን ለመፍታት የተጀማመሩ ስራዎች አሉ ብለዋል፡፡
በመጨረሻ አቶ ገረመው መድረኩ ለማዘጋጀት አስተዋፅኦ ያደረገውን አለማቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በተቋሙ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የአብክመ ፍትሕ ቢሮ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፀሐይነህ አጥናፍ የአማራ ክልል የትብብር ጥምረት የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፓርት አቅርበው ከባለድርሻ ተቋማት ተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
የአማራ ክልል ም/ቤት የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ወርቅነህ እንደግ በበኩላቸው በክልልና ከክልል በታች ባሉ አካላት በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት እንዴት ነው ልንሰራ የሚገባ የሚለውን በአንድ ማዕቀፍ ማየት፣በሌላ በኩል ክልሉ ደግሞ ከፌዴራል እና ከአጐራባች ክልሎች ጋር ምንድነው ሊሰራ የሚገባው ብሎ ለይቶ ማውጣትና ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡