Get Mystery Box with random crypto!

ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በስምንት(8) አመት ከ5 (አምስት) ወር እስራት ተቀጣ ከ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በስምንት(8) አመት ከ5 (አምስት) ወር እስራት ተቀጣ
ከሳሽ የሰዴ ወረዳ ዓ/ህግ
ተከሳሽ አቶ ደሳለኝ ገብሬ ሙኔ የተባለው እድሜ 21፣ አድራሻ ሰዴ ወረዳ ሰዴ ከተማ ፣የትምህርት ደረጃ 10ኛ ክፍል፣የቤተሰብ ሁኔታ ያላገባ ፣ስራ ሽማ ስራ
የወንጀሉ ዝርዝር አፈጻፀም ተከሳሽ በ1996ዓ.ም ተደንግጎ የወጣውን የኢ.ፌዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669(3) ለ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ግንቦት 18 ቀን 2014ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 4፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በሰዴ ወረዳ ሰዴ ከተማ ልየ ቦታው ቤተክርስቲያን መንደር እተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ የግል ተበዳይ ይልቃል ጫኔ ታሪኩን ቤት ምርግቱን ሰርስሮ በመገንጠልና በሩን ከፍቶ በመግባት የዋጋ ግምቱ 8000(ስምንት ሺህ )ብር የሆነአንድ ዩኒ ተች ስክሪን ስልክ ከ2 ሲም ካርድ ጋር ፣የዋጋ ግምቱ 900(ዘጠኝ መቶ )ብር የሆነ አንድ ትንሽ Jax ሞባይል ከሁለት ሲም ካርድ ጋር እና 3000(ሶስት ሺህ)ብር በድምሩ 11900(አስራ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ሰርቆ በመውጣት በቀን 19/09/2014ዓ.ም ሰዴ ከተማ ልዩ ቦታው 4 ኪሎ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ ከወሰዳቸው ስልኮችና ከ650 (ስድስት መቶ ሃምሳ ብር) ጋር የተያዘ በመሆኑ በፈጸመው ከባድ ስርቆት ወንጀል 5 የሰው ፣አንድ የሰነድ ማስረጃና የኢግዚቪት ማስረጃዎችን በማያያዝ የሰዴ ወረዳ ዓ/ህግ በቁጥር 698/14 በቀን 23/09/2014ዓ.ም ክስ መስርቷል፡፡
ክሱ የደረሰው የሰዴ ወረዳ ፍርድ ቤትም የተከሳሽን የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ የክስ ተቃውሞ የለኝም የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ክዶ በመከራከሩ ዓ/ህግ ይሰሙልኝ ያላቸውን ማስረጃዎች ሰምቷል፡፡በመቀጠል ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ሊከላከልና ሊያስተባብል ያልቻለ በመሆኑ የኢ.ፌዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669(3) ለ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ከባድ ስርቆት ወንጀል ጥፋተኛ ነው በማለት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/አንቀጽ 149(1) መሰረት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
የሰዴ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀን 01/10/2014ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ከዚህ በፊት በመዝገብ ቁጥር 0200275 በቀን 11/10/2013ዓ.ም የኢ.ፌዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669(3)ለ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በከባድ የስርቆት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ተቀጥቶ የነበረ በመሆኑ ልማደኛ ደጋጋሚ ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት በመያዝ እንዲሁም አንድ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት በመያዝ ተከሳሹን ከመሰል ድርጊት ይቆጠባል፣ ሌላውንም የማህበረሰብ ክፍል ያስተምራል ብሎ በማሰብ ጥፋተኛው እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ በስምንት(8) አመት ከ5 (አምስት) ወር እስራት ሊቀጣ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡