Get Mystery Box with random crypto!

'የፍትሕ ሥርዐቱ የሚዘምንበትን መንገድ አልሞ መሥራት አስፈላጊ ነው' የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

"የፍትሕ ሥርዐቱ የሚዘምንበትን መንገድ አልሞ መሥራት አስፈላጊ ነው" የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ አቶ ገረመው ገብረጻድቅ

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2014 ዓ.ም የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ከጠበቆች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በፍትሕ ሥርዐቱ ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረመው ገብረጻድቅ
የፍትሕ ሥርዐቱ የሚዘምንበትን መንገድ አልሞ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥብቅና ሥራ ለፍትሕ ሥርዐቱ መጎልበት አንድ ክንፍ ነው ያሉት አቶ ገረመው ጠበቆች ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጠበቆች ማኀበር ፕሬዚዳንት ኃይለየሱስ ደምሴ ሁሉም አካል ለፍትሕ ሥርዐቱ መሻሻል ኃላፊነት መውሰድ አለበት ብለዋል።

ጠበቆች ሥራቸውን በሚያከናውበት ወቅት ክፍተት እንዳይፈጠር በመተዳደሪያ ደንባቸው መመራት እና የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አቶ ኃይለየሱስ ባልተገባ ግንኙነት ችግር በፈጠሩ ጠበቆች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ፈቃድ መንጠቅ የሚደርስ ውሳኔ መተላለፉን አመልክተዋል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለማስወገድ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ፣ በአማራ ክልል እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ እንዲሁም የማህበሩ አባል ጠበቃ ገበያው ይታየው በፍትሕ ሥርዐቱ የሚያልፉ የክርክር ሂደቶች፣ ክርክሮች የሚዳኙበት ሁኔታ፣ የሚወስዱት ጊዜ ለፍትሕ መጓደል መንስኤ ናቸውም ብለዋል።

ፍትሕ ሲጓደል ሊመጣ የሚችለውን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሥነ-ልቦና ውድቀት ለመቅረፍ ጠበቆች ሕግ ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን በሕግ ማርቀቅ ሂደቱ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከ800 በላይ ጠበቆች ፍቃድ ወስደው አገልግሎት እየሠጡ ቢሆንም የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ጥቂት ጠበቆች ከተቀመጠላቸው የአሠራር ሥርዐት ውጭ ሲሰሩ በመገኘታቸው ለልዩ ልዩ ቅጣቶች መዳረጋቸውን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
(አሚኮ)