Get Mystery Box with random crypto!

በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎችን ከእንግልት ለመታደግ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት መፍጠር  እንደ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎችን ከእንግልት ለመታደግ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት መፍጠር  እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2015 ዓ.ም   ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደት ለመከላከል በፓዴት አስተባባሪነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራ እና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ አወቀ ዘመነ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎችን ከእንግልት ለመታደግ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አቶ አወቀ በሕገ ወጥ መልኩ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ደላላዎች መበራከታቸው ወጣቶች በሀገራቸው ሠርተው የመለወጥ እድላቸውን እንዳይመለከቱ እና ለሕገወጥ ስደት እንዲጋለጡ እያደረገ ነው ብለዋል። አቶ አወቀ ወጣቶች ከሕገ ወጥ ስደት ይልቅ በየአካባቢያቸው ያሉ የሥራ እድሎችን መመልከት አለባቸው ብለዋል።

ሕጋዊ እና ቀልጣፋ የኾነ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት  አለመኖሩም አንዱ የሕገወጥ ስደት ምክንያት ስለመኾኑ አመላክተዋል። ወጣቶች በቂ ሙያ ይዘው በሕጋዊ መልኩ የውጭ ሀገር የሥራ  ስምሪት እንዲያገኙ ለማስቻል የክልሉ ሥራ እና ስልጠና ቢሮ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ስለመኾኑም አቶ አወቀ ገልጸዋል። በክልሉ 23 ሽህ 238 ወጣቶች በ80 ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙም አመላክተዋል። ከስልጠና በኋላም ሕጋዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የሀገር ውጭ የሥራ ስምሪት ትስስር እንደሚፈጠርላቸውም ገልጸዋል።

የፓዴት ደቡብ ወሎ ዞን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወልዴ ጋሻው፤ ፓዴት ወጣቶች በሀገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል። ከስደት የተመለሱ ወጣቶች ተመልሰው እንዲቋቋሙም ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

አቶ ወልዴ ወጣቶች ሕገ ወጥ ስደትን መጠየፍ አለባቸው ብለዋል። ይልቁንም በሀገራቸው ከትንሽ ነገር ተነስተው በመሥራት የመለወጥ ልምድን ማዳበር አለባቸው ነው ያሉት።

ጥብቅ ትስስር ፈጥረው የሰዎችን ዝውውር የገንዘብ ምንጭ ያደረጉ ደላላዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ አሠራር አለመኖሩ አምራች የኾኑ የክልሉ ወጣቶች በስደት ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝም አቶ ወልዴ ገልጸዋል። 

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር ዓለም አቀፍ ወንጀል መኾኑን ገልጸዋል። ይህንን ወንጀል ለመከላከል በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት የቅንጅት አሠራር ያስፈልገዋል ብለዋል። እንደ አማራ ክልል ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ብለዋል። ወንጀሉ ተከስቶ ሲገኝም በተቀናጀ መልኩ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም  ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀሉ ተጎጅዎች ጭምር ፈቃደኛ ኾነው ስለሚፈጸም ለመከላከል የውስብስብነት ባህሪ ያለው ነው ብለዋል። ይሕንን ወንጀል በቅንጅት በመከላከል ዜጎችን ከሕገ ወጥ ስደት ለማዳን ለወጣቶች ሰፊ ግንዛቤ መፈጠር አለበትም ብለዋል። ሕዝቡ ወንጀለኞችን አሳልፍ የመስጠት ትብብር በማድረግ ዜጎችን ከዚህ አስከፊ ስደት የመከላከል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ዶክተር አያሌው አሳስበዋል።

አሚኮ