Get Mystery Box with random crypto!

በቋራ ወረዳ በአልማ የሚገነቡ ት/ቤቶችን ለመገንባት ውል ወስዶ ግንባታውን በውሉ መሰረት ያላጠናቀ | የአብክመ ፍትሕ ቢሮ ANRS JUSTICE BUREAU

በቋራ ወረዳ በአልማ የሚገነቡ ት/ቤቶችን ለመገንባት ውል ወስዶ ግንባታውን በውሉ መሰረት ያላጠናቀቀው ኮንትራከተር እና አንበሳ ኢንሹራንሰ 716,567 ብር ከ40 ሳንቲም እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት ተወሰነባቸው።

በቋራ ወረዳ መስተዳድር በአልማ አማካኝነት ከህዝብ በተሰበሰበ ሀብት በወረዳው የሚገኙ ት/ቤቶችን የማስፋፊያ ግንባታ ለመገንባት በአልማ ጉባኤ በማስወሰን ሳልፈረዲ ቁጥር 2 ት/ቤት ፣ አጋም ውሃ ት/ቤት ፣ አብተጋሆ ት/ቤት ፣ ቢኛኛ ት/ቤት እና ጉምዝ ውሃ ት/ቤትን ለማስገንባት የቋራ ወረዳ ት/ጽ/ቤት ጨረታ አውጥቶ አቶ ሙልጌታ አለነ የህንፃ ስራዎች ተቋራጭ ድርጅት ጨረታውን አሸንፎ በቀን 25/5/2012 ከተቋሙ ጋር በ 4,849,098 ብር ከ20 ሳንቲም የግንባታ ውል ወስዷል። ተቋራጩ የግንባታ ውል ሲወስድም የቅድሚያ ከፍያ ማስከበሪያ 30% እና የውል ማሰከበሪያ 10% ከአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋስትና ያቀረበ ሲሆን ተቋራጩ በውሉ መሰረት ግንባታውን አጠናቆ ለቋራ ወረዳ ት/ጽ/ቤት ባለማስረከቡ ተቋሙ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በህግ አግባብ ውሉን አቋርጧል። የወረዳው አልማ ጽ/ቤት እና ት/ጽ/ቤት በግንባታው ላይ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ውሉን በማቋረጥ ተቋራጩ የወሰደውን ቅድሚያ ክፍያ እንዲሁም የውል ማስከበሪያ 10% እና ሌሎች ከውሉ ጋር የሚከፈሉ ክፍያዎች በድምሩ 716,567 ብር ከ40 ሳንቲም አንበሳ ኢንሹራንሰ ጭምር ተከሶ ገንዘቡን እንዲከፍሉ እንዲደረግ ክሱን ለምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ የቋራ ወረዳ ት/ጽ/ቤት በመላክ የህግ ድጋፍ ተደርጎለታል።

የዞን ዐቃቤ ህግም የቋራ ወረዳ ት/ጽ/ቤት የላከውን የፍትሃብሔር ክስ በመመልከት 1ኛ ተከሳሸ አቶ ሙልጌታ አለነ 2ኛ ተከሳሸ አንበሳ ኢንሹራንሰ 716,567ብር ከ40 ሳንቲም እንዲከፍሉ ለምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቦ በመከራከር የዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የፍትሃብሄር ችሎት በቀን 23/07/2014 ዓም በዋለው ችሎት ተከሳሾች በነጠላ እና በአንድነት 716,567. 40 ብር ለቋራ ወረዳ ት/ጽ/ቤት እንዲከፍሉ የወሰነ ሲሆን የዞን ዐቃቤ ህግም በውሳኔው መሰረት እንዲፈፀም የአፈፃፀም ክሰ በመመስረት 2ኛ ተከሳሸ አንበሳ ኢንሹራንስ በቀን 0/ 09/2014 ዓም 716,567 ብር ከ40 ሳንቲም ለቋራ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ጽ/ቤት ገቢ አድርጓል።

የመንግስት የግንባታ ውሎች ፣ ፕሮጀክቶች ፣ ልዩ ልዩ ውሎች በውላቸው መሰረት እና ጥራት እንዲፈፀሙ ውል የሰጠው ተቋም በአግባቡ መከታተል ይኖርበታል።የመንግስት ሀብት ለታለመለት አላማ መዋሉን እያንዳንዱ ተቋም ክትትል ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን የመንግሥት ሀብት አላግባብ ሲባክን ፣ የግንባታ ውሎች ሲጓተቱ እና ሲቋረጡ ፣ በግዝ ሒደት ብልሹ አሰራር ሲኖር በየደረጃው ያለ የመንግስት መስሪያ ቤት ክትትል በማድረግ ዐቃቤ ህግን የህግ ድጋፍ መጠየቅ የሚገባ ሲሆን መንግስት በሚከስበትም ሆነ በሚከሰስበት የፍትሃብሔር ጉዳይ በእየደረጃው ያለ ዐቃቤ ህግ እንዲከራከርበት ቀድሞ ማሳወቅ ይገባል።

መረጃው የምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ የፍትሐብሔር የስራ ሒደት ነው።